Saturday, July 13, 2013

የኢህአዴግ የፖለቲካ ዥዋዥዌ

      የኢህአዴግ የፖለቲካ ዥዋዥዌ
እንቆቅልሽ እየሆነ የሚያስቸግረን የኢህአዴግ የፖለቲካ ዥዋዥዌ፤ በአብዛኛው ጊዜያዊ ጨዋታ ሳይሆን፤ ከራሱ ከኢህአዴግ ተፈጥሮ የሚመነጭ ነባር ባህርይ ነው። ኢህአዴግ በተፈጥሮው፤ “አንድም፤ ሁለትም ነው” ማለት ይቻላል። አንድም “አብዮታዊ” ልሁን ይላል፤ ሁለትም “ዲሞክራሲያዊ” ልሁን ይላል። አንደኛውንና ገናናውን “አብዮታዊ ኢህአዴግ”፤ ሌላኛውንና አናሳውን “ዲሞክራሲያዊ ኢህአዴግ” ብለን ልንሰይማቸው እንችላለን። ይህንን መንታ ማንነት፤ በሁሉም የኢህአዴግ አስተሳሰቦች ውስጥ ታገኙታላችሁ።

ለምሳሌ የኢኮኖሚ አስተሳሰቦቹን ተመልከቱ። አንድም፤ “ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል” እያለ የሚሰብክ ሶሻሊስት ነው። ሁለትም፤ “ያፀደቅኩት ህገመንግስት ነጭ ካፒታሊዝምን ያሰፍናል” እያለ የሚናገር ነው። በፓለቲካውስ? አንድም፤ “የቡድን መብት፤ የብሄር ብሄረሰብ መብት፤ የብዙሃን መብት” እያለ ህዝባዊነትን (ሶሻሊዝምን) ይደሰኩራል። ሁለትም፤ “የግለሰብ መብት የህገመንግስታዊ ስርአታችን አንድ ምሶሶ ነው” በማለት ይናገራል።
አንዳንዴ “ኢህአዴግ” ይነሳበታል፤ እናም ወደ ግራ አቅጣጫ ይንደረደራል። ሌላ ጊዜ ደግሞ፤ ሰከን ብሎ “ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ” ይባንናል፤ ያኔ ወደ ቀኝ አቅጣጫ ይንፏቀቃል። በእርግጥ እንዲህ በተቃርኖ ተወጥሮ እስከ ወዲያኛው መዝለቅ አይችልም። ፈጠነም ዘገየም፤ ወደ አንዱ አቅጣጫ እያመዘነ መሄዱ የማይቀር ነው (በተቃርኖ ተወጥሮ መፍረስ ወይም መፈንዳት ካልፈለገ በቀር)። ከሁለቱ ተቃራኒ አቅጣጫዎች (ከሁለቱ ተቃራኒ ማንነቶች) መካከል አንዱ እስኪያሸንፍ ድረስ ግን፤ ተቃራኒዎቹ ማንነቶች እየተፈራረቁ በዥዋዥዌ አገሪቱን ይዞ በአዙሪት መሾሩ ይቀጥላል።
ኢህአዴግና ዲሞክራሲያዊው ኢህአዴግ፤ ምን ያህል ተቃራኒ አቋሞችን እንደሚይዙ ለማየት፤ የተለያዩ ርእሰ ጉዳዮችን በማንሳት እንመልከት። በቢዝነስና በመንግስት ጣልቃ ገብነት ላይ፤ በኪራይ ሰብሳቢና በጥገኛ፤ በተቃዋሚ ፓርቲና በሚዲያ ክርክር ላይ፤ በህገመንግስትና በአገራዊ መግባባት ላይ፤ “ሁለቱ ኢህአዴጎች” በአቋም ይለያያሉ። ሌላው ይቅርና በዲሞክራሲና በአብዮት ላይ ያላቸው አቋምም ለየቅል ነው። አንዳንዶቹን ለመመልከት እንሞክር።
“ኢህአዴግ”፤ የኛ ዲሞክራሲና የፖለቲካ ምርጫ ከአሜሪካ ይበልጣል ይላል - የመራጮች ተሳትፎ በኢትዮጵያ ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ። በአሜሪካ፤ መምረጥ ከሚችለው ህዝብ መካከል ከ60 በመቶ በታች ያህሉ በምርጫ ይሳተፋል። በኢትዮጵያ ግን ከ85 በመቶ በላይ ድምፅ በመስጠት ይሳተፋል በማለት ያብራራል  ኢህአዴግ። ኮሙኒስቶች የሚያዘወትሩት አባባል መሆኑን ልብ በሉ። የአንድ ፓርቲ አገዛዝና፤ እንደ ሳዳም ሁሴን የመሳሰሉ አምባገነኖች በነገሱባቸው አገራት ውስጥ፤ ከ90 በመቶ በላይ ህዝብ በምርጫ ይሳተፍ እንደነበረ ግን አይወራም።

በአሜሪካ እንደሚታየው፤ በቀጥታ የሚተላለፍ የፓርቲዎችና የፖለቲከኞች ክርክር አስፈላጊ እንዳልሆነ የሚገልፀው “ኢህአዴግ”፤ በቀጥታ ስርጭት የህዝብ ጥያቄች ጎልተው አይወጡም በማለት ያጣጥለዋል። የፖርቲዎች ክርክር በሚዲያ ከመሰራጨቱ በፊት “ኤዲት” ሲደረግ፤ የህዝብ ጥያቄዎች ጎልተው ይወጣሉ በማለትም ይከራከራል።
“ኢህአዴግ” በበኩሉ፤ የአሜሪካ ዲሞክራሲ እጅግ የዳበረ እንደሆነና ኢትዮጵያም ቀስ በቀስ ዲሞክራሲን በመገንባት እንደምታዳብር ይገልፃል። በቀጥታ የሚሰራጭ የፓርቲዎችና የፖለቲከኞች ክርክር፤ በአሜሪካ እንደሚታየው ከጠንካራ የዲሞክራሲ ባህል ጋር የተሳሰረ እንደሆነና ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው በአድናቆት ይናገራል ኢህአዴግ”። በኢትዮጵያ ግን የዲሞክራሲ ባህል ስላልዳበረ፤ በቀጥታ የሚሰራጭ የፓርቲዎች ክርክር፤ እንደ 97ቱ ምርጫ ስሜታዊነትንና ግጭትን ይፈጥራል የሚለው  ኢህአዴግ”፤ ቀስ በቀስ ዲሞክራሲያዊ ባህል ማዳበር አለብን ይላል።
ከአንድናት ኢትዮጵያ ብሎግ


ኢትዮጵያ ክብር ለዘላለም ትኑር!

No comments: